Fana: At a Speed of Life!

አርዓያ መሆን የቻለው ብርቱ…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሥራ ብርታት እና በስኬቱ ለበርካቶች ምሳሌ መሆን የቻለው ባለታሪካችን ብዙዐየሁ ሙሉጌታ (ኢ/ር) ይባላል።

ባለታሪካችን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዲሁም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሰስቴነብል ኢነርጂ ኢንጂነሪንግ ማስተርሱን ሠርቷል፡፡

ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም የቅጥር ሥራ ፍለጋ ጊዜውን አላባከነም፤ አካል ጉዳተኝነቱም ያሰበውን ከመከወን፤ የጀመረውንም ሥራ ከማስፋት አላገደውም ።

ይህ ብርቱ ሥራ ፈጣሪ ግዙፍ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን እያመረተ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ለተለያዩ 15 ድርጅቶች ያቀርባል፡፡

ምርቶቹን ከሚያቀርብላቸው ተቋማት መካከልም፤ ጅማ፣ ቦንጋ፣ ሚዛን ቴፒ እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ማረሚያቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡

“አንድም ቀን አካል ጉዳተኝነቴ ትዝ ብሎኝ አያውቅም፤ በሥራ ላይም ጫና አላሳደረብኝም” የሚለው ብዙዐየሁ (ኢ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ ለሆኑ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግሯል፡፡

በአንድ ሥራ ብቻ ያልተገደበው ባለታሪካችን፤ የፈጠራ ክኅሎቱን በማሳደግ የቡና ገለባ እና ተረፈ ምርቶችን ወደ ከሰል የሚቀይር ማሽን በመሥራት ለደንበኞቹ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከሀገር ውስጥ ፍላጎት ባለፈ በቀጣይ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ እንዳለውም ከጅማ ፋና ኤፍ ኤም 98 ነጥብ 1 ጋር በነበረው ቆይታ አንስቷል፡፡

“ጥረት ካለ ከታሰበበት ለመድረስ የማይቻልበት ምክንያት የለም” በማለት ሁሉም ዓላማውን ለማሳካት ሊተጋ እንደሚገባ መክሯል፡፡

ተግባር ተኮር የሥራ ፈጠራ ስልጠናዎችን በመስጠት ተማሪዎችን እያበረታታ እንደሚገኝም የጅማ ዩንቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ኤፍሬም ዋቅጅራ (ኢ/ር) ጠቅሰዋል፡፡

በበሪሳ ኃ/ማሪያም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.