ጆርዳን ፍልስጤማውያንን ለመቀበል ተስማማች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጆርዳን በአሜሪካ የቀረበላትን ጥያቄ ተከትሎ ከጋዛ የሚመጡ ፍልስጤማውያንን ለመቀበል መስማማቷ ተሰምቷል፡፡
ጆርዳን ፈቃድኝነቷን የገለፀችው የሀገሪቱ መሪ ንጉስ አብዱላሂ ሁለተኛ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት ወቅት ነው፡፡
በዚህ ወቅት ንጉስ አብዱላሂ ሁለተኛ አሜሪካ ያቀረበችውን ጥያቄ ተከትሎ 2 ሺህ በችግር ውስጥ የሚገኙ የጋዛ ህፃናትን ጆርዳን በጊዜያዊነት እንደምታስጠልል ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የንጉሱን ፈቃደኝነት አድንቀዋል ነው የተባለው፡፡
አሜሪካ ፍልስጤማውያንን ወደ ተለያዩ ሀገራት በማስፈር ጋዛን ለመገንባት ማቀዷን ትራምፕ ለንጉሱ ያስረዱ ሲሆን ንጉሱ ግን በሃሳባቸው ዙሪያ አስተያይት ከመስጠት ተቆጥበዋል ተብሏል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎም በህመም እና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ 2 ሺህ የጋዛ ህፃናት ወደአማን እንደሚዘዋወሩ ቢዝነስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን መልሶ ለመገንባት እና ፍልስጤማውያን የተሻለ ህይዎት ይኖራቸዋል ባሉት እቅድ ፍልስጤማውያንን ወደ ተለያዩ ሀገራት ለማስፈር እቅድ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡
የፕሬዚዳንቱ እቅድ በአብዛኛው ሪፐብሊካን ሴናተሮች ድጋፍ ቢያገኝም ፥ ፍልስጤማውያንን እንዲያሰፍሩ የተጠየቁ ሀገራትን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የፕሬዚዳንቱን እቅድ እየተቃወሙት ይገኛሉ፡፡
በሚኪያስ አየለ