ሳይፈቀድላቸው ድሮን በሚያስነሱ አካላት በጸረ-ድሮን ቴክኖሎጂ ርምጃ እየተወሰደ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ፈቃድ ሳያገኙ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ድሮን በሚያስነሱና በሚያበሩ አካላት ላይ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ የድሮንና ሌሎች በራሪ አካላት አጠቃቀምን በተመለከተ ለፋና ዲጂታል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው÷በአዲስ አበባና አካባቢዋ ማንኛውንም አይነት ድሮን ያለ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል በቅርቡ ማሳሰቡን አስታውሷል፡፡
በተለይ ከአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ጋር ተያይዞ ቅንጅታዊ ስምሪቱን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ማንኛውንም አይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል መልዕክት የተላለፈ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ÷ብዙዎችም ይህን ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጂ ማሳሰቢያውን በመጣስ ፈቃድ ሳያገኙ ድሮን ለማስነሳትና ለማብረር ሙከራ ያደረጉ አካላትን በጸረ-ድሮን ቴክኖሎጂ በመለየት ወደ ሕጋዊ አሠራር እንዲገቡ ከማድረግ ጀምሮ ተገቢው ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመልክቷል፡፡
አገልግሎቱ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደኅንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጿል።
በተለይ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ድሮኖችና መሰል ቴክኖሎጂ ወለድ መሣሪያዎች የሚፈጥሯቸውን ስጋቶች ለመከላከል የሚያስችል በቂ የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ዝግጅት አድርጎ ወደ ስምሪት መግባቱን አስታውቋል፡፡
ከሥራ ጋር በተያያዘ ድሮኖችን መጠቀም የሚፈልግ ማንኛውም አካል በ+251 983 00 02 98 እና +251 983 00 04 01 ስልክ ቁጥሮች በመደወል ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት እንደሚችል አገልግሎቱ አሳስቧል።
ያለፍቃድ በሚኒሱ እና በሚበሩ ድሮኖች ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡