የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ በዛሬ ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ በዛሬ ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የፓርቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ 2 ሺህ 100 ተሳታፊዎች በታደሙበት በደማቅ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በትናንትናው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።
በጉባዔው 1 ሺህ 700 የድምፅ ተሳታፊዎች እንዲሁም የ15 ሀገራት ፓርቲዎች አመራርና ተወካዮችን ጨምሮ 400 የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶች በተጋባዥነት ተገኝተዋል፡፡
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ጉባዔውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ጉባዔው ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ተወካዮችን ባሳተፈና በዴሞክራሲያዊነት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም ጉባዔው መድረኩን የሚመሩ የፕሬዚዲየም አባላትን በመሰየም በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በስፋት መወያየቱንና አጀንዳዎችን መርምሮ ማጽደቁንም ተናግረዋል።
በዚህም የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት እና የስብሰባ ሥነ-ሥርዓት ደንብ ላይ በስፋት በመወያየት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል ብለዋል።
በመቀጠልም የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የኢንስፔክሽንና ሥነምግባር ኮሚቴ ሪፖርቶች ለጉባዔው ቀርበው ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ መጽደቃቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ጉባዔው በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል ነው ያሉት።
ከአንደኛ ጉባዔ ማግስት በፓርቲው በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና ፈተናዎችን ለማለፍ የተኬደበትን ርቀት በስፋት መገምገሙንም አንስተዋል።
በዚህም የብልፅግና እሳቤ እስከ ታችኛው ህብረተሰብ ክፍል መድረሱ እና እሳቤው ባህል እየሆነ መምጣቱ የተረጋገጠበት ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባዔው በነገው ዕለትም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን÷ የፓርቲ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ የአመራር ምርጫ ይደረጋል ብለዋል።
ለዚህም በዛሬው ዕለት አስመራጭ ኮሚቴ በመሰየም የዕለቱ ስብሰባ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደተጠናቀቀ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጉባዔው ለመጪዎቹ ዓመታት የሚያገለግሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሆነም ጠቁመዋል።