የጎረቤት እና የብሪክስ ሀገራት እህት ፓርቲዎች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎረቤት እና የብሪክስ ሀገራት እህት ፓርቲዎች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገለጹ።
‘ከቃል እስከ ባህል’ በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በጉባኤው መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የጎረቤት ሀገራት እህት ፓርቲዎች እና የብሪክስ አባል ሀገራት እህት ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ታድመዋል።
በተጨማሪም የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የጎረቤት እና የብሪክስ ሀገራት እህት ፓርቲዎች በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ይህን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ አሁን እየታየ ያለውን ለውጥም አድንቀው በትብብር በመስራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ለመታደም ከ15 ሀገራት የተውጣጡ የጎረቤት ሀገራት እህት ፓርቲዎች እና የብሪክስ አባል ሀገራት እህት ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።