የግድብ ማጠናቀቂያ ስራ ሳይሰራ ክፍያ በመውሰድ ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ያደረሱ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት የአነስተኛ መስኖ ግድብ የማጠናቀቂያ ስራ ሳይሰራ እንደተሰራ አስመስለው ቅድመ ክፍያ በመክፈል በመንግስት ላይ ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ያደረሱ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወሰነ።
ተከሳሾች 1ኛ የክልሉ ግብርና ቢሮ አነስተኛ መስኖ ግንባታ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ የነበረው ቴድሮስ ዳመና፣ 2ኛ የሮብሰን የውሃ ስራ ተቋራጭ ድርጀት ስራ አስኪያጅ ኢሳያስ ተካበ እና 3ኛ የሮብሰን የውሃ ስራ ተቋራጭ ድርጅት ናቸው።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1 አንቀጽ 33 እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 5 እና አንቀጽ 13 (2) ስር የተደነገገውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በዚህም ተከሳሾች የማይገባ ጥቅም ለማገኘት ወይም ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ 1ኛ ተከላሽ የክልሉ ግብርና ቢሮ በህዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም የቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ ባር አነስተኛ መስኖ ግንባታ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ሆኖ ተመድቦ በሚሰራበት ጊዜ ላይ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የሮብሰን የውሃ ስራ ተቋራጭ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲሰሩ የግብርና ቢሮው በክልሉ ካፒታል በጀት በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ የባሮ ወንዝ አነስተኛ የመስኖ ግድብን የጥገናና የማጠናቀቂያ ስራ ለማሰራት ጳጉሜ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በወጣው ጨረታ መነሻ መሰረት 3ኛ ተከሳሽ በ16 ሚሊየን 304 ሺህ 170 ብር ከ94 ሳንቲም የጨረታው አሸናፊ በመሆን በጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በሰባት ወራት ስራውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ውል ገብቶ እንደነበር በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።
በዚህም 2ኛ ተከሳሽ የግንባታ ዋና ዋና ስራዎች በሙሉ ሳይሰራ እንደተሰሩ በማስመሰል የክፍያ ሰነድ አዘጋጅቶ በ3ኛ ተከሳሽ በድርጅቱ ስም በማቅረብ 1ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ2ኛ ተከሳሽ የተዘጋጀውን የክፍያ ሰነድ በማጽደቅና የክፍያ የምስክር ወረቀት በማዘጋጀት ስራው በውል ሳይሰራ እንደተሰራ በማስመሰል ለ3ኛ ተከሳሽ ቅድመ ክፍያ እንዲፈፀም ያደረጉ መሆኑን በመግለጽ ዐቃቤ ሕግ ዝርዝር ክስ አቅርቧል።
የቦይ መሰረተ ልማት፣ የከፍታ ውሃ ማሸጋገሪያ ድልድይና የመስኖ ግድብን የጥገናና የማጠናቀቂያ ስራ በውል ሳይሰራ 2ኛ ተከሳሽ በጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም በ3ኛ ተከሳሽ ድርጅት ስም “ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተሰርቶ ስለተጠናቀቀ ርክክብ እንዲደረግ” የሚል ደብዳቤ በመጻፍ ለግብርና ቢሮ ማስገባቱ ተገልጿል።
በደብዳቤው መነሻ የመስኖ የግንባታ ስራው በውል ሳይጠናቀቅ 3ኛ ተከሳሽ 14 ሚሊዮን 206 ሺህ 806 ብር ከ24 ሳንቲም ቅድመ ክፍያ እንዲከፈለው በማድረግ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶ የተገነባው የመስኖ ግድብ ጥራት የጎደለው በመሆኑ ህብረተሰቡ የልማት ተቃሚ እንዳይሆን መደረጉና በመንግስት ላይ ጉዳት የደርስ እና በዚሁ ልክ ያልተገባ ጥቅም ያገኙና ያስገኙ መሆኑቸው ተመላክቷል።
ተከሳሾች የመንግስትና የህዝብ ጥቅም የሚጎዳ ተግባር የፈፀሙ መሆናቸው ተጠቅሶ የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኃን መምራት ሙስና ወንጀል ክስ ዐቃቤ ሕግ አቅርቦባቸዋል ከክስ ዝርዝሩ ጋር 12 የሰው ምስክር ዝርዝርና 4 የሰነድ ማስረጃ አያይዞ አቅርቧል።
ተከሳሾቹ ክስ ከደረሳቸው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን ክደው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ አሰምቷል።
ፍርድ ቤቱም ማስረጃውን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን በአግባቡ ማስተባበል አለመቻላቸውን ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል።
ከዚህም በኋላ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ያቀረቡትን አራት አራት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በዕርከን 25 መሰረት እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ከ8 ወራት ጽኑ እስራትና በ140 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
3ኛ ተከሳሽ ድርጅቱን በሚመለከት ደግሞ በ650 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።
በታሪክ አዱኛ