ብልጽግና ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት እየሰራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት እውን እንዲሆን እና የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ አቶ ሰለሞን አየለ ባደረጉት ንግግር፤ ምክር ቤቱ በሀገሪቷ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት እውን እንዲሆንና የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥም የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቷ ለዘመናት የነበውን የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህል በመቀየር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መተባበር፣ መተራረምና መፎካካርን እውን ማድረግ ያስቻለ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠሩንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጋቢት 5 ቀን 2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈራርመው ያቋቋሙት የጋራ ምክር ቤት በሀገሪቷ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ባሳዩት ቁርጠኝነት ምክር ቤቱ የሚመራበትን መመሪያ ደንብ ማጽደቅና አሰራር እና አደረጃጀቱን እስከ ወረዳ ማዋቀር መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
አመራሩም በዴሞክሲያዊ ምርጫ እንዲመረጡ በማድረግ የሰላማዊና የዴሞክራሲያዊ መድረክ ልምምድ እውን እንዲሆን መሰራት መቻሉን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ብልጽግና ፓርቲም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ሚናው ባሻገር አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአሳታፊነት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።