አየር ኃይሉ የውጊያ ዝግጁነት የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች መሰራቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ኃይሉን የውጊያ ዝግጁነት የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የኢፌዲሪ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ሎጀስቲክስ ብርጋዲየር ጄኔራል ነገራ ሌሊሳ ገለፁ፡፡
የአየር ኃይል ሎጀስቲክስ ተቋሙ የታጠቃቸውን የአቪየሽን፣ የአየር መከላከልና የምድር ድጋፍ ሰጭ ትጥቆችን ከመጠገን ጀምሮ የአየር ኃይልን የውጊያ ዝግጁነት በማረጋገጥ ለተቋሙ አሁናዊ የለውጥ ጉዞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአየር የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረጉ የግዳጅ ስምሪቶች ሁሉ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ያልተቋረጠ የሎጅስቲክ አቅርቦቶችን ተደራሽ በማድረግ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውን ምክትል አዛዡ አብራርተዋል፡፡
ሙያተኛው ከዘመኑ የአየር ሎጀስቲክስ ተልዕኮና ግዳጅ አኳያ የተቃኘ እንዲሆን በእውቀት ላይ የተመሰረቱ የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ብርጋዲየር ጄኔራል ነገራ ሌሊሳ የጥገና ሙያተኞችን አቅም ከማሳደግ በተጨማሪ የእውቀትና የቴክኖሎጅ ሽግግር እየተፈጠረ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
እውቀታችን፣ ጉልበታችን እና ውስን ሃብታችንን በመጠቀም ባከናወናቸው በርካታ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋልም ነው ያሉት፡፡
በዚህም ለታላቅ ሀገር ታላቅ አየር ኃይል የመገንባት ጉዞን ዕውን ለማድረግ በከፍተኛ ንቅናቄና ትጋት እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉም መግለጻቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡