የቅድመ ክፍያ ስማርት ቆጣሪዎች ትግበራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) በዩኒፋይድ ፕሪፔይመንት ፕሮጀክት የቅድመ ክፍያ ስማርት ቆጣሪዎች ትግበራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ይህም ደንበኞች ከፍጆታ ክፍያ ጋር ተያይዞ ያሉ ቅሬታዎች በመቅረፍ እና የደንበኞች እንግልት በማስቀረት ባሉበት ቦታ ሆነው ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ኢነርጂ መግዛት የሚያስችላቸውን ስርዓት ለመፍጠር ብሎም ተቋሙ የኢነርጂ ሽያጭ ገቢውን በአግባቡ ለመሰብሰብ ያስችላል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ 500 ሺህ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን በዘመናዊ ቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች በመቀየር ለደንበኞች አገልግሎቱን ለመስጠት እንዲያስችል ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተቋሙ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡
አሁን ላይ ከ500 ሺህ ቆጣሪዎች ውስጥ 125 ሺህ በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ ለሶስት ፌዝ ቆጣሪ ተጠቃሚ ደንበኞች ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
25 ሺህ ነጠላ ፌዝ ስማርት ቆጣሪዎች ደግሞ አዲስ አበባ ለሚገኙ ደንበኞች እየተቀየረ እንደሚገኝ ጠቁሟል።