ዓለም ባንክ ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ድጋፉን እንደሚቀጥል አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ላደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢየርድ እና ከዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ኩዋኩዋ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ በዓለም ባንክ በተገኘ ከ17 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨሰትመንት ስራዎች እተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ባንኩ በኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በግብር እና ፋይናንሺያል ዘርፎች እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎችን በተመለከተም አብራርተዋል፡፡
መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር እየፈጠረ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው፡፡
የዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢየርድ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ ያደረገውን የፋይናንሺያል ሴክተሮች እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አድንቀዋል፡፡
ማሻሻያዎቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረጉ ዓለም ባንክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡