የርዕደ-መሬት ክስተትና አሁናዊ ሁኔታ…
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሁኑ ወቅት በአፋር አዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ እና በኦሮሚያ ፈንታሌ ወረዳዎች ላይ የሚታዩትን ጂኦሎጂካል እንቅስቃሴ ከቀይ ባህር በሰሜን እስከ ሞዛምቢክ በደቡብ ባለው የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ አካል እንደሆነ ይገለፃል፡፡
ይህ የርዕደ መሬት ሁኔታ በመስከረም ወር 2017 ዓ/ም ለተወሰኑ ቀናት ከተሰማ በኋላ ከታህሳስ ወር ጀምሮ በድግግሞሽ በመጠንና በመሬት ቅርጽ ላይ የተለያዩ ገጽታዎች እያሳየ በመምጣቱ በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ የርዕደ መሬት ነክ ጉዳዮች የሳይንስ ማኀበረሰብ፣ የሰመራ፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በመሆን ሂደቱን በንቃት እየተከታተሉ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ምክረ-ሐሳቦችን በማስተላለፍ ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡
በቅርቡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት የተከሰተውን ተከታታይ ርዕደ-መሬት ሁኔታ በትኩረት እየተከታተለው መሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ባደረገው ጥልቅ ውይይት በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚፈፀሙ ተግባራትን እና ፈጻሚ አካላትን በመለየት አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን ፥ ስራዎችም በዚሁ መሰረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተነስቷል፡፡
በአፋር ክልል የርዕደ – መሬት የስጋት ወረዳዎች በሆኑት አዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች በሚገኙ 4 ቀበሌዎች (ሳቡሬ፣ ዶሐ፣ ባሌኢታ፣ ቀበና) እና በዱለሳ ወረዳ ሦስት ቀበሌዎች (ስገንቶ፣ ዱርፍሌና ከሰም ስኳር ፋብሪካ አካባቢ) በሚገኙ 7 ቀበሌዎች ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት 60 ሺህ 36 የቤተሰብ አባላት ካሏቸው 10 ሺህ 6 አባወራ እማወራ መካከል በአማካይ 90 በመቶ ያህሉ አካባቢያቸውን እንዲለቁ በማድረግ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲቆዩ እየተደረገ ነውም ተብሏል።
በኦሮሚያ ክልል የርዕደ-መሬቱ ስጋት ከሚስተዋልበት ፈንታሌ ወረዳ ቅድሚያ የተሰጣቸው 5 ቀበሌዎች 4 ሺህ 60 አባወራዎች (20 ሺህ 302 ዜጎች) ሙሉ በሙሉ አካባቢያቸውን ለቀው በጊዜያዊ መጠለያ አንዲጠለሉ ተደርጓልም ነው የተባለው፡፡
በሌላ በኩል የስጋት አካባቢ ተብለው የተለዩ ሁለት ቀበሌያት ውስጥ የሚገኙ 1ሺህ 440 አባወራ እማወራ (7 ሺህ 200 ዜጎች) ከአካባቢው እንዲነሱ ለማድረግ ከማኀበረሰቡ ጋር እየተሰራ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት በበላይነት የርዕደ – መሬት ስጋትን በሚመለከት በቅርበት የማስተባበርና የክትትል ስርዓት እያከናወነ እንደሚገኝ፤ በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሴክተር መ/ቤቶችና የአጋር አካላት ተሳትፎ እየተቀናጀ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በዋና መ/ቤትና ስጋት ባለባቸው ወረዳዎች ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ስጋት ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከላትን በማዋቀር ዕለታዊ የእቅድና የአፈጻጸም ክትትል እየተደረገ እንዳለ፤ በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩትና በተባባሪ ዩኒቨርሲቲዎች አማካይነት ዕለታዊ የርዕደ – መሬት ባህሪያቶችና ስጋቶች ምክረ-ሐሳብ እየተሰጠ እንደሚገኝና፤ በየደረጃው የተቋቋመው ማስተባበሪያ ማዕከል ከርዕደ – መሬት ነክ የሳይንስ ማህበረሰብ የሚቀርበውን የጥንቃቄ መልዕክትና ምክረ-ሃሳብ በመውሰድ ተግባራዊ እያደረገ እንዳለም ተገልጿል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑና ከመኖሪያ ቀዬያቸው ለተነሱ ክልሉና ማኀበረሰቡ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ከ70 ሺህ በላይ ወገኖች በ282 ሚሊየን ብር ወጪ ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆነ መሰረታዊ ፍላጎት የሚያሟላ የአንድ ወር ድጋፍ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፌዴራል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ በክልሉ መንግስት፣ አጋር አካላት ማህበረሰቡና ልዩ ልዩ ማህበራት አማካኝነት (መጠለያ፣ መመገቢያና አልባሳት የእንስሳት መኖ እንዲሁም የእንስሳት መድኃኒት የህክምና መስጫ ድንኳኖችንና መድኃኒት፤ የውሃ ማጠራቀሚያ የውሃ ማከሚያ ኬሚካል እየተሟላ እንዳለ ተነስቷል፡፡
ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ 1ሺህ 542 ህፃናትን ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡
በአጠቃላይ በስጋት አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰብ አካላት በሙሉ በሚመለከታቸው ተቋማት የሚሰጡ ምክረ-ሃሳቦችን ሁሉም በጥብቅ እንዲተገብሩና ከአሳሳች መልዕክቶችና ገለጻዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ ኮሚሽኑ መክሯል፡፡