ዩክሬን የሩሲያ ነዳጅ ማጣሪያን በድሮን መታች
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዩክሬን በአንድ ሣምንት ውስጥ ሁለተኛውን የሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያ በአራት ሰው አልባ አውሮፕላኖች መምታቷ ተሰምቷል፡፡
ከምስራቅ ዩክሬን በ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሩሲያ ክስቶቮ ከተማ የሚገኘውን የነዳጅ ማጣሪያ መምታቷን ነው ዩክሬን ያስታቀወቀችው።
በዚህም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።
በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተለጠፉ ቪዲዮዎች በኢንዱስትሪ ተቋም ላይ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ሲነሳ እንደሚያሳይ የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።
የአካባቢው አስተዳዳሪ ግሌብ ኒኪቲን በኢንዱስትሪ ዞኑ ላይ የሰው አልባ አውሮፕላን ፍርስራሾች ወድቀው እንደነበር ቢገልጹም ፥ በስፍራው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰ ተናግረዋል።
የሩሲያዋ ከተማ የስሞልንስክ ገዢ ቫሲሊ አኖኪን በቴሌግራም ገጽ እንዳሉት ፥ ምንም እንኳ በሰው ህይዎት ላይ ጉዳት ባይከሰትም በመሠረተ ልማት ላይ “ግዙፍ” የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት አድርሷል ብለዋል፡፡
ከድሮኖቹ አንዱ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን ለመምታት ሲሞክር በጥይት ተመትቷልም ነው ያሉት።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሶስተኛው ዓመት እየተቃረበ ሲሆን ፥ መካረሩ ግን እየተባባሰ ሄዷል፡፡
ሩሲያ የዩክሬን ምስራቃዊ ክፍል ወደሆነች እስትራቴጂካዊ ከተማ ፖክሮቭስክ እየቀረበች ሲሆን ፥ በአንጻሩ የዩክሬን ሃይሎች በነሐሴ ወር ጥቃት በከፈቱበት በሩሲያ ምዕራብ ኩርስክ ክልል ውስጥ 100 ካሬ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ግዛት መያዛቸውን ቀጥለዋል።