የተከናወኑ የፖሊሲ ለውጦች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ከፍ ማድረጋቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲፕሎማሲው መስክ የተከናወኑ የፖሊሲ ለውጦች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ከፍ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በዲፕሎማሲው መስክ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና የተገኙ ስኬቶችን በማስመልከት አምባሳደር ብርቱካን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ በመተግበር ከጎረቤት ሀገራትና በቀጣናው ትብብርን በማስቀደም መስራቷን አጠናክራ መቀጠሏን አንስተዋል።
ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በሚሰጠው የፖሊሲ አቅጣጫ መሰረት በጋራ ተጠቃሚነትና በሰጥቶ መቀበል መርህ የልማት ትስስሮችን የማጠናከርና ቀጣናዊ ሰላምን የማስጠበቅ ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በንግድና የምጣኔ ሃብት ትስስር፣ በኤሌክትሪክና የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሁም በውሃ እና በሌሎች መስኮች የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን ተወጥታለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄም በሰጥቶ መቀበል መርህ የጋራ ልማት፣ እድገትና ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ አጠቃላይ በዲፕሎማሲው መስክ የተተገበሩ የፖሊሲ ለውጦች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ከፍ ማድረጋቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏም በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘ የላቀ ስኬት እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ለዜጎች ቅድሚያ በመስጠት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ በርካታ ወገኖችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ መከናወኑንም አንስተዋል።