ፕሮግራሙ የሆስፒታሎችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ይጠቅማል- ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም የሆስፒታሎችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ጠቃሚ ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
ሚኒስቴሩ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም የሥድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
ሚኒስትሯ በግምገማው ማጠቃላይ ወቅት እንደ ሀገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት በመገንባት የአገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የማሕበረሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሻሻልና የሆስፒታሎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ፕሮግራም ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
ፕሮግራሙ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተቀርፆ እስከ 4ኛው ምዕራፍ ድረስ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በሆስፒታሎች መካከል ጠንካራ ትስስርና መደጋገፍን በመፍጠር የሕብረተሰቡን የሕክምና የአገልግሎት ፍላጎት እርካታ ለማሳደግ ምቹ አሠራርን እንደፈጠረ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡