Fana: At a Speed of Life!

10 ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ራስ ገዝነት ለማሸጋገር እየተሰራ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በመጪው ሁለት ዓመት ውስጥ 10 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ራስ ገዝነት ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለፁ፡፡

ሚኒስትሩ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እውነተኛ የእውቀት ማዕከል እንዲሆኑ እየሰራ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች እውነተኛ የትምህርት ተቋም ሆነው የእውቀት፣ የምክንያታዊነት፣ የሰላማዊና የሰለጠነ ውይይት፣ የሀቀኝነትና የእውነተኝነት ማዕከል ሊሆኑ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ ወደ 47 ዩኒቨርሲቲዎችን መገንባት ቢቻልም በዚያው ልክ ጥራት ላይ አለመሰራቱ ግን ትውልድ ላይ ክፍተት ፈጥሯል ነው ያሉት።

ለዚህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሪፎርም ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከሪፎርሙ መካከል በ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተከናወነው የምዘና ሥራ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ካሉ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በመሆን ለሀገር ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነው፤ በቀጣይ በመማር ማስተማርና በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ይበልጥ እንዲሰራ አሳስበዋል።

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.