የድሮን ቴክኖሎጂ ፖሊስ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችላል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ፖሊስ ውስጥ የተዋወቀው የድሮን ቴክኖሎጂ ማዕከል ወጣት የፖሊስ ኦፊሰሮች የቴክኖሎጂ ስልጠና አግኝተው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ።
ኮሚሽሩ በዋናው መስሪያ ቤት የተደራጀውን የድሮን ፓይለት ማሰልጠኛ ማዕከል መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በወቅቱ እንደገለጹት ፥ አዲስ የገቡት ድሮኖች ከከተማ ፀጥታ ቁጥጥር ባሻገር የድንበር ጥበቃን ጨምሮ የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በቀላሉ መቆጣጠር ያስችላሉ።
መንግስት በሰጠው ትኩረት ፖሊስ ዘመናዊ ትጥቆች እንዲኖሩትና ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ የወንጀል መከላከል ስራዎችን በብቃት ለመስራት እንዲችል ተደርጓል ማለታቸውን ከፌደራል ፖሊስ የተገነው መረጃ አመላክቷል።
እንደ አፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ያሉ መድረኮች ሲኖሩ ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን ዘግቶ ቪአይፒዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል የራሱ የሆነ ኮማንድ ኮንትሮል ያለው ዘመናዊ “Road block” ተሽከርካሪም በዛሬው ዕለት ተመርቆ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡