Fana: At a Speed of Life!

ፓርቲው የገባውን ቃል በተግባር በመፈፀም ቃሉን ባህል አድርጎ እየሰራ ነው – አቶ ጌቱ ወዬሳ

አዲስ አበባ፣ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባኤ የገባውን ቃል በተግባር በመፈፀም ቃሉን ባህል አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ የፓርቲው የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለፁ።

በሐረሪ ክልል ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ እስከ ወረዳ መሰረታዊ ድርጅት ድረስ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው የሁለተኛው ጉባኤ ቅድመ ኮንፍረንስ መጠናቀቁን በብልፅግና ፓርቲ ኃላፊው ገልጸዋል።

አቶ ጌቱ ወዬሳ ኮንፍረንሱ መጠናቀቁን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ፓርቲው በአንደኛው ጉባኤው ለህዝብ የገባውን ቃል እውን በማድረግ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበና እያስመዘገበ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ግዜ ጀምሮ በጥራት በማከናወን ቀድሞ የነበረውን የስራ ባህል የቀየረ ፓርቲ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይ ህብረብሄራዊነትና አንድነትን በማጎልበት በአመራሩ መካከል በተፈጠረው የወንድማማችነት እና እህትማማችነትን መንፈስ የሀገሪቱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች በመጠገን ብሎም ማህበራዊ እሴቶችን በማጎልበት አሻጋሪ ፕሮግራሞችን ቀርፆ በመተግበር በሁሉም ዘርፍ ተጨባጭ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ በተፈጠረው ጠንካራ የስራ ባህል በልማት ስራዎች፣ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እመርታዊ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ሲካሄድ የነበረው የቅድመ ጉባኤ ኮንፍረንስም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን ይበልጥ በማጎልበት ለቀጣይ ተልዕኮና ስኬት ለአመራሩ አቅም የተፈጠረበት መሆኑን አክለዋል።

በክልል ደረጃ በተካሄደው የማጠቃለያ ኮንፍረንስ በቀጣይ በሚካሄደው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የሚሳተፉ አባላትን በዲሞክራሲያዊ መንገድ በመምረጥ መጠናቀቁን መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.