ጋምቤላ ክልል በ6 ወራት ከ27 ኩንታል በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ27 ኩንታል በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት አስታወቀ።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ጊሎ ÷ መንግስት ከወሰዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መካከል የወርቅ ማዕድን ሃብት ልማቱ አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።
ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ስኬቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ በመግለጽ በክልሉ ያለውን ሰፊ የወርቅ ማዕድን ሀብት ልማት በማዘመንና ከብክነት በመታደግ ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በባህላዊ፣ በልዩ አነስተኛና በወርቅ አምራች ኩባንያ የተመረተ ከ2 ሺህ 747 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።
የወርቅ ምርት አሰራሩ እየዘመነ መምጣቱ ሀብቱ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች እንዳይበዘበዝ በማድረግ ለሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይ ስድስት ወራትም ቀደም ሲል የነበረውን ዕቅድ በመከለስ 2 ሺህ 200 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት መታቀዱን አብራርተዋል።