በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ65 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በመስኖ የማልማት አቅም ተገነባ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከመደበኛ እርሻ በተጨማሪ በዓመት ከ65 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በመስኖ የማልማት አቅም መገንባቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለፁ።
አቶ ማስረሻ በላቸው እንዳሉት ፥ ባለፉት ሦስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ውጤት ለማምጣት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንና ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል።
በክልሉ መታረስ የሚችል 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት እንዳለ ገልጸውም÷ከሦስት ዓመት በፊት በዓመት በዋና ዋና ሰብሎችና በሆልቲካልቸር ምርቶች ይለማ የነበረው መሬት 590 ሺህ እንደነበረና በአሁኑ ወቅት ወደ 948 ሺህ ሄክታር ማደጉን አንስተዋል፡፡
ከመደበኛ እርሻ በተጨማሪ በዓመት ከ65 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በመስኖ የማልማት አቅም መገንባቱን ጠቁመው÷ ግብርናውን ለማዘመን በተሰሩ ሥራዎችም ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደረገ ጥረትም በኩታ ገጠም ይለማ የነበረ 2 ሺህ 340 ሄክታር መሬት ወደ 143 ሺህ ሄክታር አድጓል ነው ያሉት።
በእነዚህ ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራም 929 ሚሊየን ችግኞችን በአርንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በመትከል 137 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በወተት፣ በማር፣ በዓሣና በዶሮ ልማት ሥራዎች በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መምጣቱንም አስረድተዋል።