ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)ከ25 ሺህ ብር በላይ ሀሰተኛ ባለ 200 ብር የገንዘብ ኖቶችን ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሶሰት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ክስ መመስረቱን የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በክፍለ ከተማው ወረዳ 8 ተክለኃይማኖት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሀሰተኛ ባለ 200 ብር ኖቶች በ100 ብር ህጋዊ ብር ለመሸጥ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በተደረገ ክትትል እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ታውቋል፡፡
በተደረገባቸው የአካል ፍተሻም ከ25 ሺህ ብር በላይ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶች መያዛቸው መረጋገጡ መገለፁን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተገቢውን ምርመራ የማጣራትና መዝገብ የማደራጀት ተግባሩን በማጠናቀቅ ክስ እንዲመሰረትባቸው ለክፍለ ከተማው ዐቃቤ ህግ መዝገቡ መቅረቡ ተገልጿል፡፡