ከደረሱ አደጋዎች 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተቻለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 6 ወራት ከደረሱ አደጋዎች 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ በአዲስ አበባና አካባቢው 244 አደጋዎች ያጋጠሙ ሲሆን÷ ከእነዚህም ውስጥ 144ቱ የእሳት አደጋዎች ናቸው ተብሏል፡፡
የደረሱትን አደጋዎች ለመቆጣጠር የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ በአደጋ ውስጥ የነበሩ የ19 ሰዎችን ሕይወት መታደግ መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡
ከደረሱት አደጋዎችም 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ከውድመት ማዳን የተቻለ ሲሆን÷በአንጻሩ ከ370 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ደግሞ መውደሙ ተጠቅሷል፡፡
በልዩ ልዩ አደጋዎችና ምክንያታቸው ባልታወቁ አደጋዎች 46 ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ መገኘቱንም የኮሚሽኑ መረጃ አመልክቷል፡፡