በፈታኝ ሁኔታዎች አመርቂ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መመዝገባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፈታኝ ሁኔታዎች አመርቂ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ተመዝግበዋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ፡፡
አምባሳደር ነብያት ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ ባለፉት ስድስት ወራት በውጭ ግንኙነት የተሰሩ ዋና ዋና ሥራዎችን እና ወቅታዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን የዳሰሱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በማራመድ ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውን እና በቀጠናው ሰላም ማስከበር ላይ ያላት ሚና እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
ከሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር ያስቻሉ ከ128 በላይ የከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝት መደረጉንም በመግለጽ እነኚህም ወዳጅነትን ለማጠናከር የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅሞች እና ወቅታዊ አቋሞች ለማስረፅ ያስቻሉ እንደሆኑ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ባለፉት ስድስት ወራት ከነበሩ ስኬቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መስክ የሀገራችንን ሚና ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ 28 ሺህ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ታቅዶ 33 ሺህ ዜጎችን መመለስ ተችሏል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ከተለያዩ ሀገራት ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ሥራዎች መሰራታቸውም የተገለጸ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ ለ968 የአጎራባች ሀገራት ተማሪዎች ነፃ የከፍተኛ የትምህርት ዕድል መስጠቷም በመግለጫው ተነስቷል፡፡