ኢንቨስትመንት ባንኮች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን ለመቀላቀል ዝግጅቶቻቸውን እያጠናቀቁ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በርካታ ኢንቨስትመንት ባንኮች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን ለመቀላቀል ዝግጅቶቻቸውን እያጠናቀቁ መሆኑ ተጠቆመ።
ሙዓለ ንዋይ ( ሃብት) የምናፈስባቸው ሰነዶች ወይም ኢንቨስትመንቶችን እንደ ባለቤትነትን የምናረጋግጥበት ሰነዶች ገበያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሲሆን፤ በአብዛኛው አክሲዮን፣ የመንግስት ቦንድ፣ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ፣ የኩባንያዎች ቦንድ እና ሌሎች ቦንዶች ወደ ማዕከላዊ ቦታ መጥተው የሚገበያዩበት መድረክ ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ዕድገት ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው የታመነበት ይህ ርምጃ መንግስትና የግሉ ዘርፍ ለሚያከናውኗቸው ኢንቨስትመንቶች ካፒታል ለማሰባሰብ አቅም የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን እዉን ለማድረግ ባለፉት አመታት የካፒታል ገበያን ከማቋቋም ጀምሮ አዋጅ በማውጣትና ሌሎች ሁኔታዎችን ለማሟላት ሲሰራ የቆየ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቆ ተከፍቷል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ይህንን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለመቀላቀል በርካታ ኢንቨስትመንቶች ፍላጎት አሳይተዋል።
አሁን ላይም ስድስት የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ባንኮች የሰነደ መዓለ ንዋዮች ገበያን ለመቀላቀል ዝግጅቶቻቸውን እያጠናቀቁ መሆኑን ነው ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል የተናገሩት፡፡
በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታትም ዝግጅቶቻቸውን እንደሚያጠናቅቁና ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው