ተሽከርካሪ አስመጪዎች የኃይል መሙያ ሳይተክሉ በሥራ ላይ አይሠማሩም ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተሽከርካሪ አስመጪና የሚገጣጥሙ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ሳይተክሉ በሥራ ላይ መሰማራት እንደማይችሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከ400 በላይ ተቋማት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እያስመጡና እየገጣጠሙ መሆናቸውን የገለጹት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሀሰን÷ ሁሉም የኃይል መሙያ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ሆቴሎች፣ የነዳጅ ማደያዎች እና የግል ባለሃብቶች በቻርጂንግ መሰረተ ልማት ላይ በስፋት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ሚኒስቴሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት ለከተሞች አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት በመኪና ማቆሚያዎች የኃይል መሙያ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወርቁ ደስታ ናቸው፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ ማደያዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያ ለመቀየር ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ