በባቱ የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቅቋል
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ ከተማ የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ም/ ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ እንዳሉት፥ በከተማው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል።
ለዚህም በክልልና በከተማ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዘርፈ ብዙ የዝግጅት ሥራ መከናወኑን ነው ያስረዱት።
በበዓሉ ለመታደም ለሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች አይረሴ ትዝታዎችን እንዲያሳልፉ የተለያዩ መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል፡፡
በከተማዋ የጥምቀት በዓልን በደምበል ደሴቶች በድምቀት ለማክበር አነስተኛ ጀልባዎችን ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የባቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አሕመዲን እስማኤል በበኩላቸው፥ በበዓሉ ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተገቢውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በባቱ ከተማ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ የቱሪስት መስህብ፣ ታሪክና ባህል ለጎብኚዎች ለማስተዋወቅ መሰራቱንም ጠቁመዋል።
ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በደምበል ሐይቅ ዙሪያ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡
ከበዓሉ ጎን ለጎን የመኪና ውድድርን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ሁነቶች እንደሚካሄዱም ከንቲባው ጠቁመዋል።
ስለሆነም በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጥምቀት በዓልን በባቱ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመላኩ ገድፍ