ኢትዮጵያዊቷ ተማሪ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆነች
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)ኢትዮጵያዊቷ አሲያ ኽሊፋ የዘንድሮው “ሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር” ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆና ተመርጣለች፡፡
የሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ዓመታዊ የስልጠና መርሐ-ግብር ከሁዋዌ ታዋቂ የማህበራዊ ኃላፊነት ስራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ዓላማውም በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣት ተማሪዎችን በአጭር ጊዜ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን አረዳዳቸውን ማሳደግ ነው ተብሏል።
በዚኅም መርሐ-ግብሩ ባለፈው ሣምንት የ2025 የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ዓለም አቀፍ አምባሳደሮችን መርጦ አሳውቋል።
ከተመረጡት 12 አምባሳደሮች መካከልም የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ የሆነችው አሲያ ኽሊፋ ትገኛለች።
የአሲያ የዓለምአቀፍ አምባሳደር ሆና ለመመረጧ በሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር 2024 መርሐ-ግብር ስኬታማ ተሳትፎ ማድረጓ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡
ይህም በፈረንጆቹ 2025 በቻይና ውስጥ በሚካሄደው የአይሲቲ ታለንት ዲጂታል ጉብኝት በአካል እንድትሳተፍ፣ የተግባር ልምድ እንድታገኝና በሌሎች ትልልቅ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች ላይ ተገኝታ የቴክኖሎጂ ተግባራዊ እውቀት እንድትካፈል እድል ይሰጣታል ተብሏል፡፡
አሲያ የዓለምአቀፍ አምባሳደር ሆና መመረጧ በፕሮግራሙ ውስጥ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መሰል ተሳትፎ ትልቅ ምዕራፍ ነው ተብሏል፡፡
በማህበረሰቧና ከዚያም በላይ ዲጂታል ቴክኖሎጂንና ፈጠራን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነትም እንደሚያሳይ ተመላክቷል።