የአፈር ሀብታችንን ለብልጽግናችን ለማዋል እንረባረብ- ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተፋሰስ ልማታችንን በማስፋት የአፈር ሀብታችንን ለብልጽግናችን ለማዋል መረባረብ አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገነዘቡ፡፡
የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሀገራዊ ንቅናቄ መጀመሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ግብን ለማሳካት በየዓመቱ ከ14 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በማሳተፍ መጠነ ሰፊ የተፋሰስ ልማት ተግባራትን በማከናወን እመርታዊ ለውጥ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብትና የተፋሰስ ልማትን በመተግበራችን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ቁርጠኝነታችንን አሳይተናል ሲሉም ነው የገለፁት።
በዚህም የተራቆቱ አካባቢዎች ማገገማቸውን፣ የአፈር መከላት መቀነሱን እና የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን አብራርተዋል፡፡
አርሶ አደሩ የተፋሰስ ልማቶችን በመጠበቅና በባለቤትነት በመያዙ የንብ ማነብ፣ የእንስሳት ርባታ፣ የመስኖ ልማት እና የፍራፍሬ ልማትን በመተግበር ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዘርፉ እስከ አሁን ያስመዘገበችው ስኬት÷ በመንግሥት አመራር፣ በሞያተኞች፣ በኅብረተሰቡና በልማት አጋሮች ተሳትፎ የተገኘ ድምር ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ዓመት በ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት እንደሚካሄድም አመላክተዋል፡፡
ይህን በማሳካትም አፈራችንን ለብልጽግናችን ለማዋል ሁሉም አካላት በትጋት እንዲረባረብ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።