በመዲናዋ ሊመዘበር የነበረን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ማዳን ተቻለ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በህገ ወጥ መንገድ ሊመዘበር የነበረ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ሃብት ማዳን መቻሉን የከተማዋ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷በመዲናዋ ብልሹ አሰራሮችን ከመቅረፍ አንጻር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
በተለይም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለማስተካከል በትብብር መሠራቱን አንስተዋል።
ባለፉት አምስት ወራትም በ3 ሺህ 933 ጉዳዮች ክሶች ቀርበው የፍርድ ቤት ክርክሮች እንደተደረጉ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 1ሺህ 314 መዝገቦችን በመከራከር በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያገኙ መደረጉን ነው ያስረዱት።
ቢሮው በ1 ሺ 266 መዝገቦች ማሸነፋን ጠቁመው ÷ በዚህም መንግስት ሊያጣው የነበረ 1ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በመዲናዋ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ተግባራትን ከስር መሠረታቸው ለማድረቅም ነዋሪዎች ጥቆማ በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በመላኩ ገድፍ