Fana: At a Speed of Life!

ወደ ውጭ ከተላኩ የእንስሳት ተዋጽዖዎች ከ54 ሚሊየን ዶላር በላይ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የሥጋና ዕርድ ተረፈ ምርቶች እና ሌሎች የእንስሳት ውጤቶች 54 ነጥብ 22 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሣህሉ ሙሉ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ወደ ውጭ ከተላከ 9 ሺህ 886 ነጥብ 58 ቶን የበግና ፍየል ሥጋ፣ የዳልጋ ከብት ሥጋ፣ የዓሣ ምርት፣ የዕርድ ተረፈ ምርት 52 ነጥብ 59 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል፡፡

በተጨማሪም 586 ነጥብ 58 ቶን የተቀነባበረ ማር፣ የሰም ምርት፣ የወተት ተዋጽዖ እና የዶሮ ምርት 1 ነጥብ 63 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ሥድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ 10 ሺህ 473 ነጥብ 16 ቶን የእንስሳት ተዋጽዖ እና ሌሎች የእንስሳት ውጤቶች 54 ነጥብ 22 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 5 ሺህ 822 ቶን ምርት ለውጭ ገበያ ቀርቦ 32 ነጥብ 25 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን አውስተው÷ በተላከ ምርት መጠንም ሆነ በተገኘ ገቢ ረገድ የዘንድሮው አፈጻጸም ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.