ኢኮኖሚው በግሉ ዘርፍ እንዲመራ በሚያደርጉ ርምጃዎች ስኬት መመዝገቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢኮኖሚው በግሉ ዘርፍ እንዲመራ ለማድረግ በተወሰዱ ርምጃዎች ለውጦች መምጣታችውን የብሔራዊ ባን ገዥ ማሞ ምኅረቱ ገለጹ፡፡
አቶ ማሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አዘጋጅነት በሚቀርበው ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” ፕሮግራም ቀርበው በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ሂደትና ተስፋዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ለውጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ሲመጡ መልከ ብዙ ችግሮችን የተሸከመ ኢኮኖሚ ነበር ብለዋል።
በዚህም የፖሊሲ እና ብዝኃ የኢኮኖሚ የዕድገት አማራጮችን መሰረት ያደረገ የሀገር በቀል መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን አውስተዋል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሪፎርም ጥሩ ጅማሮ የነበረው ቢሆንም ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ኢኮኖሚያዊ ጫና ማሳደራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈተናዎች ውስጥ ሆኖም በማይበገር አቅም በመቀጠል ውጤት አስመዝግቧል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢኮኖሚው በግሉ ዘርፍ እንዲመራ ለማድረግ በተወሰዱ ርምጃዎች ለውጦች መምጣታችውንም አንስተዋል፡፡
በዚህም ከለውጡ በፊት 70 በመቶ ገደማ የባንኮች ብድር ለመንግስት ብቻ እንደነበረና አሁን ላይ ግን 80 በመቶ ገደማ የሚጠጋ ብድር ለግሉ ዘርፍ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሁለተኛ ምዕራፍ ጥልቅ እና በርካታ ዘርፎች የያዘ ሁሉን አቀፍ እና ቅንጅታዊ መዋቅር ጠንካራ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ስርዓቱ ወደ ገበያ መር ስርዓት መግባቱ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት እንዲጨምር ማድረጉን እና የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ክምችትንም ማሳደጉን ጠቁመዋል።
ዘላቂ የዕዳ አስተዳደር እንዲኖር እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎችም ጤናማ የዕዳ አስተዳደር ለመፍጠር አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል፡፡
ጥብቅ የገንዘብ እና ፊሲካል ፖሊሲዎች ትግበራም ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ የራሱን ሚና መጫወቱን ነው ያስረዱት።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ታሪካዊ፣ አይነኬ የተባሉ ዘርፎች ላይ ድፍረት የተሞለባት ውሳኔ የተላለፉበት፣ የተቀናጀ፣ በጥናት እና በጥንቃቄ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።
ሪፎርሙ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍ አቅም በማሳደግ፣ የስራ እድል በመፍጠርና የገቢ መሰብሰብ አቅምን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
በዘላቂነት ቀጣይነት ያለው ዕድገት በመፍጠር ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ውጤት እንደሚያመጣ አሁን ላይ ካሉ አመላካቾች በመነሳት መናገር ይቻላል ነው ያሉት።