እስራኤልና ሃማስ በዚህ ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5/.2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እስራኤልና ሃማስ በተያዘው ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ የአሜሪካ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ገለጹ።
የጸጥታ አማካሪው ዛሬ በነጩ ቤተ መንግስት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ÷ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመፈረም ጫፍ ደርሰዋል ብለዋለ።
“ቃል እየገባሁ ወይም ግምት እያስቀመጥኩ አይደለም፤ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርበናል፤ስምምነቱ በዚህ ሳምንት ይጠናቀቃል” ብለዋል አማካሪው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጉዳዩ ዙሪያ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና ከኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አልታኒ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ጄክ ሱሊቫን ተናግረዋል።
አማካሪው አክለው በቅርቡም ፕሬዚዳንት ባይደን ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ጋር በስልክ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
ኳታር፣ ግብጽና አሜሪካ በእስራኤልና ሃማስ መካከል እየተካሄደ ያለውን የተኩስ አቁም ድርድር እየመሩ መሆናቸው ይታወቃል።