ጥምቀትን በጎንደር በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሀገር ውስጥና ከውጪ ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ አበበ ላቀው እንዳሉት÷ወደ ታሪካዊቷ ጎንደር ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡
ጥምቀትን በጎንደር ለሚያሳልፉ እንግዶች ከቱሪዝም መስሕቦች በተጨማሪ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለከተማዋ ውበት የፈጠሩ መሆናቸው ምቹ አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንግዶች በቆይታቸው በከተማዋ ያሉ የቱሪስት መስሕቦችን በመጎብኘት አይረሴ ትዝታዎችን እንደሚያሳልፉም አብራርተዋል፡፡
ጥምቀትን በጎንደር ማክበር በሚከናወኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ከየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ሃሴትን የሚፈጥር ድንቅ ትሩፋቶች በከተማዋ መኖራቸውን ገልጸዋል።
ጎንደር ከጥንት ጀምሮ የሥነ-ሕንፃ፣ ሥነ-ሰዕል፣ ሥነ-ትምህርት፣ ኪነ ጥበብ፣ የሲራራ ንግድ ማዕከል፣ የስልጣኔ ቀንዲል እና የዘመናዊ አኗኗር ተምሳሌት ከተማ መሆኗን አውስተዋል፡፡
ዛሬም ለከተማዋ ፈርጥ ከሆነው ዓለም አቀፍ ቅርስ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥት እድሳት በተጨማሪ የኮሪደር ልማት ሥራ ለከተማዋ ውበት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጎንደር የቱሪዝም ማዕከል ከመሆኗ ባሻገር ለኢንቨስትመንት ምቹ አማራጮች እንዳሏት ገልፀው÷በከተማዋ በኢንቨስትመንት መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ከተማ አስተዳደሩ ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ስለሆነም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ ዜጎች በጎንደር ጥምቀትን ታድመው ጥሩ ጊዜ ከማሳለፍ ባለፈ በከተማዋ ኢንቨስት እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በነብዩ ዮሃንስ