የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለምስኪኗ እናት ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራት ልጆችን ያለአባት እያሳደገች ለምትገኘው እናት የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል፡፡
ፋና ዲጂታል ታሕሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም “ከሕመም ጋር አራት ልጆችን ያለአባት የማሳደግ የእናትነት ብርቱ ፈተና …” በሚል ዘገባ መስራቱ ይታወሳል፡፡
በዚህም እናት ፀሐይ ተሻለ አሁን ላይ ካለባት ሕመም ጋር አራት ልጆችን ማሳደግ ከአቅሟ በላይ በመሆኑ እርዳታ እንደምትሻ መናገሯ ይታወቃል፡፡
በተለይም ልጆቿ የምገባ አገልግሎት እንዲያገኙ እና ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላት ጠይቃለች፡፡
ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እናት ፀሐይ እና አራት ልጆቿ ያለባቸውን ችግር በመረዳት የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል፡፡
በዚህ መሰረትም እናት ፀሐይ እና ልጆቿ በመዲናዋ አራት ኪሎ በሚገኘው የምገባ ማዕከል ውስጥ የምገባ አገልግሎት በቋሚነት እንዲያገኙ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በተጨማሪም ቤተሰቡ በከተማዋ በሚገኙ የጤና ተቋማት ነጻ የሕክምና አገልገሎት እንዲያገኝ በጤና መድሕን እንድትታቀፍ መደረጉን ነው ያስታወቀው፡፡
ከዚህ ባለፈም አራቱ ልጆች ትምህርታቸውን በሚገባ እንዲከታተሉ አስፈላጊውን የትምህርት ግብዓት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡
እናት ፀሐይ ተሻለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ችግሯን ተረድቶ ላደረገላት ፈጣን የእርዳታ ምላሽ ምስጋና አቅርባለች፡፡
ከልጆቿ ጋር አራት ኪሎ በሚገኘው የምገባ ማዕከል የምገባ አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸውን ገልጻ፤ ይህም ትልቅ እፎይታ እንደፈጠረላት ለፋና ዲጂታል ተናግራለች፡፡
ህጻናት ልጆቿ በበኩላቸው፥ የምገባ አገልግሎት ማግኘታቸው ትምህርታቸውን በሚገባ እንዲከታተሉ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ለዚህም የተቸገሩት ደራሽ ለሆኑት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቅርበዋል።
እናት ፀሐይ ወገኖቿ ያለባትን ችግር ተረድተው እያደረጉላት ለሚገኘው ድጋፍ አመስግናለች።
በመላኩ ገድፍ