የዴንማርክ መንግስት የኢትዮጵያን ልማት ማገዝ እንደሚፈልግ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እየሰራችው ያለውን ስራ የዴንማርክ መንግሥት ማገዝ እንደሚፈልግ የሀገሪቱ ልዕልት ቤኔዲክቴ አስትሪድ ገለጹ፡፡
በልዕልቷ የተመራው የልዑካን ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉብኝት በማድረግ ከአፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ እና በዴንማርክ መካከል ስለሚኖረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ መክረዋል።
ሀገራቱ ቀደም ሲል የነበራቸውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች አብሮ ለመስራት ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላት አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ አካታች የሆነ ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለትምህርት በተለይም ለሴቶችና ህጻናት እንዲሁም ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
ልዕልት ቤኔዲክቴ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እየሰራችው ያለውን ስራ የዴንማርክ መንግሥት ማገዝ ይፈልጋል ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።