Fana: At a Speed of Life!

ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የህክምና ግብዓት በመሰወር የተከሰሰው ግለሰብ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ድርጅት ተረክቦ ለኦሮሚያ ክልል ማስረከብ የነበረበትን የህክምና ግብዓት ሳያስረክብ ሰውሮ ለግል ጥቅም በማዋል የተከሰሰው ግለሰብ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወሰነ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ድርጅት ሾፌር በነበረው መስፍን መክብብ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ስር እንዲሁም በሙስና አዋጁ አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2/ሀ እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ በሚል ሁለት ክሶችን አቅርቦበት ነበር።

አንደኛው ክስ ላይ ተከሳሹ የድርጅቱ ሾፌር ሆኖ በሚሰራበት ወቅት ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ድርጅቱ ለጤና ተቋማት የሚያከፋፍላቸውን መድሐኒቶችና የህክምና ግብዓትን ለማድረስ በተሰጠው ሀላፊነት መነሻነት ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም በወጭ ማድረጊያ ደረሰኝ የተረከበውን 9 ሺህ 500 እሽግ የእጅ ጓንቶችን፣ 1 ቤዚን ኪድኒ እና 2 እስፕሪተር የተባለ የህክምና መሳሪያ፤ 2 ሚዘን ቢኤም ትሪፕል የህክምና መሳሪያ አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 5 ሚሊየን 515 ሺህ 227ብር ከ30 የሆኑ የህክምና መሳሪያዎችን ለኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ እንዲያደርስ ከተረከበ በኋላ ሳያስረክብ ለራሱ ወስዶ የሰወረ በመሆኑ ከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበት ነበር።

በ2ኛ ክስ ደግሞ ተከሳሹ ከድርጅቱ ወደ ኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ለማድረስ በሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም በወጭ ማድረጊያ ደረሰኝ የተረከባቸውን የህክምና መሳሪያዎች ለጤና ቢሮው ባላስረከበበት ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ለደም ባንክና የህክምና ግብዓቶች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በመረካከቢያ ደረሰኝ እንዳስረከበ በማስመሰል ሀሰተኛ የመረካከቢያ ሰነድ ለኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ድርጅት ያቀረበ በመሆኑ በፈጸመው በሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሷል።

ተከሳሹ የክስ ዝርዝር ከደረሰውና በንባብ ከተሰማ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦበታል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ተመልክቶና መርምሮ በክሱ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ተግባር መፈጸሙን ማረጋገጡን ጠቅሶ ሁለቱ ክሶች ተጣምረው እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሹ የቀረበበትን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮና የተከሳሹን 4 የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በዕርከን 22 መሰረት በ6 ዓመት ጽኑ እስራትና በ6 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.