በአማራ ክልል የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት 960 ሚሊየን ብር ተመደበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት እንዲቻል ከተለያዩ የሀብት ምንጭች በማሰባሰብ 960 ሚሊየን ብር መመደቡን አስታውቋል።
የቢሮው ሃላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ(ዶ/ር) እንዳሉት÷የክልሉን ሰላም ከማጽናት በተጓዳኝ የገበያ ዋጋን የማረጋጋት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
በግማሽ ዓመቱ በሕገ-ወጥ ግብይት የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ከ55 ሺህ 454 በላይ ነጋዴዎች ሕገ-ወጥ ግብይት ሲፈጽሙ መያዙን ገልጸዋል።
በዚህም እንደ ጥፋታቸው ከማስጠቀቂያ እስከ ማገድ እንዲሁም በሕግ ተጠያቂ እስከ ማድረግ የደረሱ ርምጃዎች ተወስደዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል 960 ሚሊየን ብር ከተለያዩ የሀብት ምንጮች በማመቻቸት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለተጠቃሚው በማቅረብ የገበያ መረጋጋትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።