ሪች ዲጂታል ኩባንያ በአሽከርካሪ ፈቃድ አሰጣጥና ሌሎች ዘርፎች መሠማራት እፈልጋለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቱ ሪች ኩባንያ በኢትዮጵያ በአሽከርካሪ ፈቃድ አሰጣጥ፣ በተሽከርካሪ ምዝገባ ሥርዓት እና በዘርፉ ባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ መሠማራት እፈልጋለሁ አለ፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ዑመር ሁሴን (ዶ/ር) የተመራ ከሀገሪቱ ኩባንያዎች የተውጣጡ አባላትን የያዘ የኢኮኖሚ ልዑክ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ጋር ተወያይቷል፡፡
በዚሁ ወቅትም እያደገ የመጣው ሀገራዊ ኢኮኖሚ፣ የመንግስት ድጋፍና የታክስ ማበረታቻ፣ በዘርፉ በቂ የሰው ኃይል መኖር ለኢንቨስትመንት ምቹ ከሚባሉ ሁኔታዎች መካከል መሆናቸው ተብራርቷል፡፡
ለኢንቨስትመንት ከተመረጡ ዘርፎች መካከልም የወደብ ልማት፣ የሎጂስቲክስ ማዕከላት ግንባታ፣ የባቡር መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት፣ በአቪዬሽን ዘርፍና በትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ የተመቻቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ቀርበዋል፡፡
ኩባንያው በኢንቨስመንት ቢሳተፍ የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ከማጎልበት በተጨማሪ ካሉት አስቻይ ሁኔታዎች አንፃር አዋጭ እንደሚሆን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በሚያስችሉ የአሽከርካሪዎች ፈቃድ አሰጣጥ፣ ተሽከርካሪ ምዝገባና ምርመራ ስራዎች ላይ ቢሳተፉ ድጋፍ ይደረጋል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በቀጣይ በሚገነባው ግዙፍና ስማርት አውሮፕላን ማረፊያ በሚዘረጋ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ስርዓት እና በከተማ ስማርት ፓርኪንግ ስራዎች ላይ ተጨማሪ የኢንቨስትመት ዕድሎች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡
የሪች ዲጂታል ኩባንያ ተወካዮች በበኩላቸው÷ የአሽከርካሪ ፈቃድ አሰጣጥና የተሽከርካሪ ምዝገባ ስርዓትን ጨምሮ በዘርፉ ባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ለመሳተፍ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡