Fana: At a Speed of Life!

በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ልዩ ተወካይ እና በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮ ኃላፊ የኢትዮጵያና ሶማሊያ የጋራ መግለጫን አደነቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ልዩ ተወካይ እና በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ኃላፊ አምባሳደር ሞሐመድ ኤል አሚን ሱፍ የኢትዮጵያና ሶማሊያን የጋራ መግለጫ መቀበላቸውን አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ የጋራ ጥቅሞቻቸው በሆኑ የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ከትናንት በስቲያ ተወያይተዋል፡፡

በዚህም የሁለቱ ሀገራትን ወንድማማች ሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ምክክር ማድረጋቸውን በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ ተመላክቷል።

ሀገራቱ የነበራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና ወደነበረበት ለመመለስና ለማጠናከር መስማማታቸውም ይታወቃል።

የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ፣ በትብብር ለመምራትና ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮቻቸውን ለመፈጸምም ባለብዙ ወገን እና ቀጣናዊ ፎረም እንደሚያስፈልጋቸው በወቅቱ መክረዋል፡፡

ይህን አስመልክቶ ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ስምምነቱን አድንቆ፥ ኢኮኖሚያዊ ውኅደትን ለማጎልበት፣ ለዲፕሎማሲያዊ ትስስርና ለቀጣናዊ መረጋጋት ብሎም ለጋራ ብልጽግና አስተዋጽዖው የጎላ መሆኑን ገልጿል።

ስምምነቱን ከሶማሊያ ሕዝብ ፍላጎትና ከአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የበለፀገች አፍሪካ ራዕይ ጋር በማጣጣም የሶማሊያን የሰላም ጥረቶች እና ቀጣናዊ አጋርነቶችን ለመደገፍ ተልዕኮው ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡

ቀጣናዊ መረጋጋት ዕውን እንዲሆን ሁለቱ ሀገራት መተማመንና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸውም አመላክቷል፡፡

ቀጣናዊ ግንኙነትን ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባትን ለማሳደግ እና ዕድገት ለማምጣት የተቀናጀ ጥረትን በማጠናከር በትብብር መሥራት እንደሚገባም መሪዎቹ መግባባት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡

በሀገራቱ መካከል ያለውን የደኅንነት ዘርፍ ትብብር ማስቀጠልና ማጠናከር እንደሚገባም መወያየታቸውን የጋራ አቋም መግለጫቸው ያመላክታል፡፡

የሀገራቱ የጸጥታ አካላት ትብብራቸውን በማጠናከር በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን መሥራት እንደሚገባቸው መሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን በሁለቱ ሀገራት መካከል ማጠናከር እንደሚገባ የመከሩ ሲሆን÷ ንግድን እና የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት የመሰረተ ልማት ትስስርን ለማሳደግ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

የአንካራ ስምምነትን በቁርጠኝነት በመፈጸም ወዳጅነትና ትብብርን ለማጠናከር መስማማታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በስምምነቱ መሰረት የተቀመጠውን የቴክኒክ ስምምነት ለመፈጸም መግባባት ላይ ተደርሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.