በኦሮሚያ ክልል ከ10 ሚሊየን በላይ የመማሪያ መጻሕፍት ተሰራጩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል10 ሚሊየን በላይ አዳዲስ የመማሪያ መጻሕፍት ለተማሪዎች መሰራጨታቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የእቅድና በጀት ዝግጅት ዳይሬክተር ሃሰን እንድሪስ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በክልሉ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የመማሪያ መጻሕፍት ጥረት እንዳይከሰት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የመምህራን መምሪያ መጻሕፍትን በቅድሚያ በማሳተም ለሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲሰራጩ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም ባለፉት አምስት ወራት ለ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች 6 ሚሊየን 472 ሺህ 18 መማሪያ መጻሕፍት መሰራጨታቸውን አንስተዋል፡፡
አዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 25 ሚሊየን የ1ኛ ደረጃ ትምህርት መማሪያ መጻሕፍትን ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በትምህርት ሚኒስቴር የታተሙ 3 ሚሊየን 574 ሺህ 327 መማሪያ መጻሕፍት ለ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች መሰራጨታቸውን አመልክተዋል፡፡
ከ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ውስጥ የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች በተወሰነ መልኩ የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት እንዳለባቸውም አቶ ሃሰን ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ