ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ የገቡት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ሲደርሱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች የጋራ ጥቅሞቻቸው በሆኑ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን የሁለቱ ሀገራትን ወንድማማች ህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ምክክር ማድረጋቸውን በጋራ ያወጡት የአቋም መግለጫ አመልክቷል።
በዚህም ሀገራቱ የነበራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና ወደነበረበት ለመመለስና ለማጠናከር መስማማታቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅርበት በትብብር ለመምራትና ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮቻቸውን ለመፈጸም ባለብዙወገን እና ቀጣናዊ ፎረም እንደሚያስፈልጋቸው በትኩረት መክረዋል።
መሪዎቹ ቀጣናዊ መረጋጋት ዕውን እንዲሆን ሁለቱ ሀገራት መተማመንና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው አረጋግጠዋል።
ቀጣናዊ ግንኙነትን ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባትን ለማሳደግ እና የጋራ ዕድገት እንዲመጣ የጋራ ጥረትን በማጠናከር በትብብር መስራት እንደሚገባም ተግባብተዋል።
በሀገራቱ መካከል ያለውን የደህንነት ዘርፍ ትብብር ማስቀጠልና ማጠናከር እንደሚገባም መወያየታቸውን ያመለከተው የጋራ የአቋም መግለጫው፤ በቀጣናው የአክራሪ ታጣቂ ቡድኖችን ስጋት ለማስወገድ የሀገራቱ የጸጥታ አካላት ትብብራቸውን በማጠናከር ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን መስራት እንደሚገባቸው መሪዎቹ መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን በሁለቱ ሀገራት መካከል ማጠናከር ጠቀሜታ እንዳለው የመከሩ ሲሆን፤ ንግድን እና የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት የመሰረተ ልማት ትስስርን ለማሳደግ ተስማምተዋል።
በመጨረሻም የአንካራ ስምምነትን በቁርጠኝነት በመፈጸም ወዳጅነትና ትብብርን ለማጠናከር የተስማሙ ሲሆን፤ በአንካራው ስምምነት መሰረት የተቀመጠውን የቴክኒክ ስምምነት ለመፈጸም መግባባት ላይ ደርሰዋል።