የካፒታል ገበያ የዜጎችን ሕይዎት የሚቀይር ዘርፍ እንዲሆን በትኩረት ይሠራል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን ጥቅል ኢኮኖሚ የሚደገፍ እና የዜጎችን ሕይዎት የሚቀይር ዘርፍ እንዲሆን በትኩረት ይሠራል ሲሉ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልኩ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን ትናንት በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን፥ በማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይም የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት ዋና ዳይሬክተሯ እንዳሉት፥ ባለፉት ዓመታት ከመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫዎች፣ ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም እና ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፎች በመነሳት የካፒታል ገበያ የማደራጀት ስራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡
በዚህም ትልቁ ትኩረት የነበረው ግልጽ የሆነ የካፒታል ገበያን የሚመራና የሚቆጣጣር የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደነበር ጠቅሰው፥ የካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248 ጸድቆ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
የህግ ማዕቀፉ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እና ገበያውን የሚያገናኙ ተቋማት እንዲተዋወቁ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
አዋጁ ገበያውን ለማቀላጠፍ የሚያመቹ ተቋማትና ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ የሚያስችል የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋቱን አመልክተዋል።
በተለይም በኢንቨስትሮች መካከል በአካል ይደረግ የነበረውን የሙዓለ ሰነዶች ግብይት በቴክኖሎጂ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
አዋጁን ተከትለው የወጡ መመሪያዎች ኢንቨስተሮችን ይጎዱ የነበሩ ችግሮች ለመቅረፍና ለውሳኔ የሚያግዛቸውን በቂና ጥራታቸውን የጠበቁ መረጃዎች እንዲያገኙ የሚያስችል የአሰራር ማዕቀፍ መፈጠሩንም አስረድተዋል።
ባለስልጣኑ በዋናነት የኢንቨስትመንት ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በቀጣይ በሙዓለ ሰነድ አቅራቢ ዋና ኢንቨስተሩ የሚታመን የካፒታል ገበያ ለመገንባት በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በካፒታል ገበያው የባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር፣ በርካታ ምርቶች እና አገልግሎቶች ለገበያው እንዲቀርቡ እና ሁሉን አሳታፊ ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ካፒታል ገበያ የሁሉም ለሁሉም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ÷ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እና የግሉ ዘርፍን ጨምሮ ሁሉም ሰው እንዲሳተፍ የሚያስችሉ አሰራሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን ጥቅል ኢኮኖሚ የሚደገፍ እና የዜጎችን ሕይዎት የሚቀይር ዘርፍ እንዲሆን በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የተለያዩ የንግድ ዓይነቶችን ታሳቢ በማድረግ ሦስት ልዩ ልዩ የገበያ ዓይነቶችን የሚያቀርብ ሲሆን÷ እነርሱም የአክሲዮን ገበያ፣ የዕዳ ሰነድ ገበያ እና የአማራጭ ገበያ ናቸው፡፡