Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ ለቴሌ የመለሱትን ስልክ ቁጥር ተጠቅሞ ከግለሰቦች መሬት ለማሰጠት በሚል ገንዘብ የተቀበለው በእስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣ የሆኑ ግለሰብ ለቴሌ የመለሱትን የቀድሞ ስልክ ቁጥር በመጠቀም ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በማዘጋጀት ባለስልጣን ነኝ በማለት ለሰባት ግለሰቦች በቴሌግራምና በኢሞ መልክት በመላክ የኢንበስትመንት መሬት እና ቦታ ይመቻችላችኋል በማለት ለጉዳይ ማስፈጸሚያ ገንዘብ በባንክ እንዲላክለት ያደረገውና በሙስና ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ መልካ አያና ላይ በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም ተደራራቢ ሰባት ዝርዝር ክሶችን አቅርቦበት ነበር።

በዚህም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር (3) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል እና በሙስና አዋጁ አንቀጽ 28 ንዑስ ቁጥር 3 ስር እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 33 እና አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 ለ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ማለትም በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ምንጩን ለመደበቅ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሚል ክስ አቅርቦበታል።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሹ በመስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ያለ አግባብ መበልጸግ ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ክ/ከ ከመልካ ጋፋርሳ ወረዳ ሀሰተኛ መታወቂያ በማውጣትና በመጠቀም በመስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቱሉ ጃሞ ቅርንጫፍ እና ከአዋሽ ባንክ አብዲ ኖኖ ቅርንጫፍ በሀሰተኛ ስም ባወጣው የነዋሪነት መታወቂያ የባንክ ሂሳብ መክፈቱ በክሱ ላይ ተመላክቷል።

በ2015 ዓ.ም የመንግስት ሰራተኛ ሳይሆን የመንግስት ሰራተኛ እንደሆነ በማስመሰል ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ያልተገባ ሀብት ለማግኘት በማሰብ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑ ግለሰብ ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረና ለቴሌ መልሰውት በአጋጣሚ እጁ የገባውን ስልክ ተጠቅሞ በኢሞና በቴሌግራም ወደ ተለያዩ ሰባት ባለሀብቶች ተከሳሹ እራሱን ባለስልጣን በማስመሰል ለመኖሪያ እና ለኢንቨስትመንት ቦታና መሬት እየተመቻቸላቸው እንደሆነ ገልጾ መልዕክት ይልካል።

ግለሰቦቹ ስልክ ሲደውሉለት ስልኩን አንስቶ “የባለስልጣኑ የጽ/ቤት ሰራተኛ ነኝ” በማለት መሬቱና ቦታው እየተመቻቸላችሁ እንደሆነ በመግለጽ መልስ ይሰጣል።

በዚህ መልኩ አሳሳች ቃላቶችን በመጠቀምና በማግባባት በሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በከፈታቸው የባንክ ሂሳቦች የመሬት ካርታ እና የቤት ግምት ገንዘብ ላኩ በማለት በተለያዩ ጊዜ በተለያዩ መጠኖች በአጠቃላይ 448 ሺህ 200 ብር እንዲላክለት አስደርጓል።

ተከሳሹ በተጨማሪም በሙስና ወንጀል የተቀበለውን ገንዘብ ወይም ንብረት ምንጭ ለመደበቅ በማሰብ የራሱን ፎቶ ግራፍ ተጠቅሞ በእለቱ የሀሰት የነዋሪነት መታወቂያ በማውጣት በሐምሌ 7 ቀን 2015 እና በመስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም ገላና ባዳዳ በሚል ስሙ ተሽከርካሪ ገዝቶ በኦዳ የተሽከርካሪ ማሰልጠኛ በሚል ተሽከርካሪውን ሲሰራበት የተያዘ መሆኑ በክስ ዝርዝሩ ተጠቅሷል።

ተከሳሹ በዚህ መልኩ የቀረበበት ክስ ዝርዝር ከደረሰው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃል በመስጠቱ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦበታል።

ፍርድ ቤም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ በተከሰሰባቸው ድንጋጌዎች ስር እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል አለመቻሉን ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎ፤ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመመርመርና በመያዝ ተከሳሹን በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በሙስና ወንጀል የገዛው ተሽከርካሪ ተሽጦ ለግል ተበዳዮች ብሩ እንዲመለስ እንዲሁም የሚተርፈው ገንዘብ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.