Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስትሩ ከኖርዲክ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ተቀማጭ ከሆኑ የኖርዲክ ሀገራት ከሆኑት የኖርዌይ፣ ስዊድን እና ፊንላንድ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከኖርዲክ ሀገራት ጋር ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላት ያወሱት ሚኒስትሩ÷ ይህንም አጠናክራ ለመቀጠል እየሰራች መሆኗን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በፖለቲካው እና ኢኮኖሚው መስክ እየተተገበሩ ስለሚገኙ የለውጥ ስራዎችም ገለጻ አድርገዋል፡፡

ለውጭ ባለሃብቶች እየተፈጠረ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም የኖርዲክ ሀገራት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው÷ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ያለበትን ሁኔታም አብራርተዋል፡፡

አምባሳደሮቹ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አረንጓዴ ምጣኔ ሃብትን ለመገንባትና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የምታከናውናቸውን ስራዎች አድንቀዋል።

ሀገራቱ በቡድን እና በተናጠል ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙት በማስቀጠል በሂደት ላይ የሚገኙ የለውጥ ስራዎችን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡

የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ በኢትዮጵያ ለግል ባለሃብቶች የተፈጠሩ አዳዲስ የኢቨስትመንት እድሎችን በመጠቀም ረገድ የኖርዲክ ሀገራት ኩባንያዎች ተሳትፎን ለማሳደግ እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን ለማረጋገጥ በተለይም በሱዳን እና ሶማሊያ የምታደርጋቸውን ተሳትፎዎች እንደሚደግፉም ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.