በርዕደ መሬቱ ዙሪያ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎችና ተግባራት ላይ አቅጣጫ አስቀምጠናል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የርዕደ- መሬት ክስተቶችና የተሰጡ ምላሾችን በመገምገም ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎችና ተግባራት ላይ አቅጣጫ አስቀምጠናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች የርዕደ-መሬት ክስተት በተመለከተ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ሃሳብ፥ በስብሰባው የሳይንስ ማህበረሰቡ አካላትና የሁለቱ ክልሎች አመራሮችም እንዲሳተፉ መደረጉን ጠቁመዋል።
ከመስከረም 2017 ዓ/ም ጀምሮ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካል በሆኑ አካባቢዎች የተከሰቱ የርዕደ-መሬትና ንዝረት ስጋቶች በልዩ ትኩረት መከታተል የሚገባን መሆኑን ተግባብተናል ብለዋል፡፡
የክስተቱ ድግግሞሽና ስፋት በአካባቢው በሚኖሩ ዜጎች ላይ ባለው ተፅዕኖ ምክንያት ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በማመን በጋራ ግብረ ሀይል የተሰሩ የቅድመ አደጋ መከላከል ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን መገምገማቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የፌዴራልና የክልል መዋቅሮች የተቀናጀ የአደጋ ስጋት ምላሽ እየሰጡ መሆኑንና የሳይንስ ማህበረሰቡ ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለ መረጃ የሰጠ መሆኑንም መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኩል አጋር አካላትና የሚመለከታቸው ዘርፎች የቅድመ መከላከል ስራውን በትኩረት መደገፋቸውን አንስተዋል አቶ ተመስገን፡፡
በአስቸኳይ ስብሰባው የርዕደ- መሬት ክስተቶችና የተሰጡ ምላሾችን በዝርዝር በመገምገም በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎችና ተግባራት ላይ አቅጣጫ አስቀምጠናልም ብለዋል፡፡
እስካሁን በቅድመ መከላከል ውጤታማ ስራው ለተሳተፉ አካላትንም አመስግነዋል።