መንግስት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ድርጊቶችን እየተከታታለ እርምጃ ይወስዳል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ድርጊቶችን እየተከታታለ እርምጃ ይወስዳል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አሳሰቡ።
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያ ተከትሎ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ገና ግማሽ አመት ሳይሞላ ለሀገሪቷ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስገኘ ነው ብለዋል።
ህዝቡንም ተጠቃሚ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን እየለወጡት መሆኑን በቅርቡ በሚኒስትሮች ደረጃ በሁሉም ክልሎች የተደረገው ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አረጋግጧል ሲሉም ገልጸዋል።
መንግስት ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ እነዚህን ማጽናት፣ ዘላቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛዉንም አይነት ድርጊቶች መንግስት እየተከታታለ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በመልዕክታቸው ገልጸዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
እንደ ዓለም አቀፉ የፔትሮል ዋጋ መረጃ የጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት የአለም አቀፉ የነዳጅ መሸጫ አማካይ ዋጋ በሊትር 1.25 የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ በሊትር በ0.805 የአሜሪካን ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡ ይህ የሚያመለክተው በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ አማካይ የመሽጫ ዋጋ የ35 በመቶ ቅናሽ ያለው መሆኑን ነው፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች አኳያም ካየነው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ ለምሳሌ በኬንያ 1.351፤ በሩዋንዳ 1.136፤ በኡጋንዳ 1.299፤ በታንዛንያ 1.127 የአሜሪካን ዶላር በሊትር በተመሳሳይ ወቅት እየተሸጠ ይገኛል፡፡
እጅግ ደሃ በሚባሉት እንደ ማላዊ በ1.459፣ ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብልክ 1.746 የአሜሪካን ዶላር በሊትር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከ1.3 የአሜሪካን ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የሰሞኑን የነዳጅ ጭማሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን የእግር እሳት የሚሆንባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደተለመደው በባንዳነት ተግባራቸው ተጠምደዋል። እነሱ የሚኖሩባቸው ሀገሮች የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ፈጽሞ አይታያቸውም። ራሳቸውን ለህዝቡ አሳቢና ተቆርቋሪ ሌላውን ደግሞ ለህዝቡ ችግሮች ደንታ ቢስ አድርገው ያቀርባሉ። ይህን የሚያደርጉት እዉነታዉን ስለማያዉቁ ሳይሆን ድብቁ ባህሪያቸው እንደይገለጥ ነዉ።
ተሳስተዉ እንኳን በየአካባቢዎቹ ስላለዉ በጎ የልማት እንቅስቃሴ፣ የሰላም ሁኔታ፣ በህብረተሰብ መካካል መግባባት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን አያነሱም፡፡ ለምን ቢባል ይህ ሃሳቦችን ማመንጨት፣ ጥናትና ፈጣራ፣ ተጨባጭ አብነትና የሀሳብ ልዕልናን ይጠይቃል፡፡ እነሱ ይህ የላቸዉም፡፡ በየአካባቢው የተፈጠሩ ትናንሽ ክስተቶች በወሬ ለቃሚዎቻቻዉ አማካይነት እየቃረሙ ቆርጦ በመቀጣል እኩይ ፍላጎታቸዉን ማሳካት ነዉ፡፡ የሚያተርፉት ከግጭት፣ ከሁከትና ግርግር ነዉ፡፡ ሰው መረጃ የሚያገኝም አይመስላቸውም። ነውር የሚባል ነገር በደጃቸው አልዞረም። ነፃ ገበያ እና በነፃ ገበያው ውስጥ የመንግስት ሚና ሚዛን መጠበቅ መሆኑ ለነሱ ምንም ነዉ።
በነጻ ገበያ ዉስጥ ይቅርና በሶሻሊስት ስርዓት መንግስት እንዲያደርግ የማይገደድባቸዉ ጉደዮችን በማንሳት መንግስትን ይከሰሉ፡፡ መረጃዎችን በማዛባት ለራስ እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ የቱንም ያህል ርቀት አይወስድም።
መንግስት ልማትን ለማፋጠን የሚወሰዱ እርምጃዎች በማህበረሰቡ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገነዘባል። በጥንቃቄ መፈፀም እንደሚገባም ያምናል። ለዚህም አቅዶ እና አልሞ የህብረሰቡን ዘላቂ ጥቅም መሠረት አድርጎ ይሠራል፡፡ ሸክሙን በመጋራት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ይረዳል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ መንግስት ለነዳጅ፣ ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለመድሃኒትና መሰል የጤና ጉዳዮች ወዘተ ከፍተኛ የሚባለውን ድጎማ እያደረገ ነው። በዓመት ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ያደርጋል። መንግስት መደበኛ ተግበራትንም ያከናውናል። ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ፍጥነት እና ፈጠራን መሠረት ያደረጉ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑና የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች እና የልማት ፕሮግራሞችን እውን እያደረገ ነው።
በተለይም የሰብል ምርት (የስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽለ፣ገብስ፣ሩዝ፣ ጤፍ)፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢንሼቲቮች ወደ ሁሉም አካባቢዎች ወርደው በውጤታማነት እየተተገበሩ ነው። የኮሪደር ልማቱም የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥኑ ከተሞችን እየገነባ ነው።
የገጠሩን የአኗኗር ሁኔታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ ስራም ተጀምሯል። የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያውን ተከትሎ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ገና ግማሽ አመት ሳይሞላ ለሀገሪቷ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስገኘ ነው። ህዝቡንም ተጠቃሚ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን እየለወጡት መሆኑን በቅርቡ በሚንስትሮች ደረጀ በሁሉም ክልሎች የተደረገው ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አረጋግጧል።
መንግስት ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ ነው። እነዚህን ማጽናት፣ ዘላቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል።
አጋጠሚዉን በመጠቀም ህብረተሰቡ ላይ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛዉንም አይነት ድርጊቶች እየተከታታለ እርምጃ ይወስዳል፡፡