Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ሥርዓት አዋጅ ፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጉባዔ የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት ሥርዓት ለመደንገግ የተዘጋጀ አዋጅን በሁለት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡

የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አይሻ ያህያ÷ማደያዎች ያልተቆራረጠ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስገደድ ነዳጅ በማደያ ውሰጥ እያለ የሽያጭ አገልግሎት ያለማቋረጥ የሚል ድንጋጌ በአዋጁ መካተቱን ገልጸዋል፡፡

የተሸከርካሪውን ጉዞ በቴክኖሎጂ ለመከታተል እንዲቻል ማንኛውም የነዳጅ ውጤቶች አጓጓዥ ተሸከርካሪ ጂፒኤስ የመግጠም ግዴታ እንዳለበት በአዋጁ ተደንግጓል ብለዋል፡፡

የነዳጅ ውጤቶች ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ አንጻር ስትራቴጂክ ምርቶች በመሆናቸው አቅርቦታቸው፣ ክምችታቸው፣ ስርጭታቸውና ደህንነታቸው አለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ እንደተዘጋጀም ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶች ከአስመጪ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የአቅርቦትና ስርጭት እንዲሁም በነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሰንሰለት ውስጥ እየታዩ ያሉ ህገ-ወጥ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር በማስፈለጉ አዋጁ ወጥቷልም ነው ያሉት፡፡

የነዳጅ እና ኢነርጅ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሀርላ አብዱላሂ በበኩላቸው÷ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አሁን ላይ እየታዬ ያለውን ህገወጥነት ለመቆጣጠር ጠበቅ ያለ ህግ እንደሚያስፈልግ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

መንግስት በሚያስቀምጠው ታሪፍ አለመሸጥ በዘርፉ እየተስተዋሉ ካሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ መሆኑን በመግለጽ ይሄም አዋጁ ላይ በግልጽ ድንጋጌ እንዲቀመጥ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የምክር ቤት አባላትም መንግስት ማደያዎች ወደገበያ ለመግባት የሚያደርጉትን ሂደት ቀላል ማድረግ ላይ ትኩረት ቢያደርግ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ 838/2006 አዋጅ ላይ ከነዳጅ ውጤቶች ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ክፍተቶች እንደነበሩበት የተገለጸ ሲሆን÷የፀደቀው አዋጅ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚከሰተውን ብክነትና በነዳጅ ዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የመንግስትና የህዝብ ንብረትን ለማስመለስ የነበረውን የሕግ ክፍተት የሚሞላ የንብረት ማስመለስ አዋጅን አፅድቋል፡፡

አዋጁ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ንብረት ማስመለስ የሚያስችሉና የሕግ-ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው።

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.