የገና በዓል የላሊበላ ከተማ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ መነቃቃት መፍጠሩ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮ የገና በዓል ባለፉት ዓመታት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ሴክተር በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡
በዓሉ ካለፈው ዓመት የበለጠ እንግዳ የተገኘበት፤ በታቀደው መሠረትም በስኬት የተጠናቀቀ በመሆኑ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል ሲሉ የአሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ ገልጸዋል፡፡
በዓሉ የአካባቢውን ሰላማዊ ሁኔታ በተግባር አሳይቷል፤ ለቀጣይ የቱሪስት ፍሰት እና የቱሩዝም ተጠቃሚነት እንዲፈጠርም መሠረት ጥሏል ሲሉ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አገልግሎት ሰጭ አካላትም ባለፉት ዓመታት አጥተውት የነበረውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የመለሰ በዓል መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
ላሊበላ ከተማ እና አካባቢው ሰላማዊ መሆኑን ለገና በዓል የታደሙ ጎብኝዎች እና እንግዶች ይመሰክራሉ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ የኑሮው መሠረት ቱሪዝም መሆኑን በአግባቡ ስለሚገነዘብ ዘርፉን የሚያስተጓጉልበትን ሁኔታ እንደማይፈልግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላሊበላን እና አካባቢውን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው