አገልግሎቱ ከ443 ሺህ በላይ ጉዳዮችን በማስተናገድ 1 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር አገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥር 01፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አምስት ወራት 443 ሺህ 147 ጉዳዮችን በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ዓለምሸት መሸሻ÷ ለተገልጋዮች ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የወረፋ ችግርን የሚፈታ አዲስ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል።
ባለፉት አምስት ወራትም በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች 443 ሺህ 147 ጉዳዮችን በመቀበል 719 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ማስተናገድ መቻሉን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ 16 ቅርንጫፎች ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽት 1 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመው÷ በተጠቀሰው ጊዜ ከተሰጡ አገልግሎቶች 1 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል አገልግሎቱ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እያከናወነ እስካሁን 44 ሺህ ዜጎች መታወቂያውን እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ተቋሙ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለአገልግሎት እንደ ቅድመ ሁኔታ መጠቅ መጀመሩን ገልጸው÷ ይህን ተከትሎም በሃሰተኛ ሰነድ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየቀነሱ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
ወንጀልን በጋራ ለመከላከልም ከክልሎች፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከተለያዩ የፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ