Fana: At a Speed of Life!

የጢያ ትክል ድንጋይ አካባቢን ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በሚልቅ ወጪ ለማልማት የዲዛይን ሥራ ተጠናቋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጢያ ትክል ድንጋይ ዓለም አቀፍ መካነ-ቅርስ አካባቢን ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በሚልቅ ወጪ ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሳሙኤል መንገሻ ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ክልሉ ባለው የመስኅብ ሐብት ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

ከእነዚህ ሥራዎች መካከል አንዱ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ውስጥ የሚገኘውን የጢያ ትክል ድንጋይ ዓለም አቀፍ መካነ-ቅርስ አካባቢን ማልማት መሆኑን ጠቁመው÷ የዲዛይን ሥራ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል፡፡

እስከ አሁንም የመንገድ ከፈታን ጨምሮ መሰል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አጠቃላይ ሥራውን በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅ መታቀዱን እና በሕዝቡ፣ ባለሃብቱ፣ በመንግሥት እና አጋር አካላት ትብብር የሚሸፈን ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ ከምባታ ዞን የሀምበርቾ 777 ኢኮቱሪዝም በተሻለ ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም÷ በአካባቢው ተጨማሪ የዲዛይን ማሻሻያ፣ የሎጅና የሆቴሎች ግንባታ በማከናወን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡም ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁን ነው ያስረዱት፡፡

እንዲሁም የጊቤ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚለሙ የቱሪዝም መስኅቦች ተለይተው የዲዛይን ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የዲዛይን ሥራው እንደተጠናቀቀም በተለያዩ አካላት ትብብር ወደ ማልማት ምዕራፍ እንገባለን ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.