Fana: At a Speed of Life!

በሀሰተኛ ዲግሪ ተቀጥሮ በዋና ስራ አስኪያጅነት ሲሰራ የነበረ ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀሰተኛ ዲግሪ ተቀጥሮ በዋና ስራ አስኪያጅነት ሲሰራ የነበረ ግለሰብ በተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ድርጊት በእስራት እና በገንዘብ እንዲቀጣ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወሰነ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ቡራዩ ከተማ ነዋሪ ጉተማ ሄዳ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር (1) እና (2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፉን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦበት ነበር።

በዚህም ተከሳሹ የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አዲስ ፋና ጠቅላላ ሸቀጣ ሸቀጥና ሆቴሎች ንግድ አክሲዮን ማህበር በሕዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው ክፍት የስራ መደብ ማስታወቂያ ተከሳሽ ለውድድር ሲመዘገብ ተገቢው የትምህርት ዝግጅት እንደሌለው እያወቀና ይህንኑ ሁኔታ በመሰወር ማለትም በሐምሌ 25 ቀን 2001 ዓ.ም በዲግሪ መርሐ-ግብር ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው በማስመሰል ሰነዱን ለድርጅቱ ማቅረቡ ተጠቅሷል።

ከጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በድርጅቱ የንግድ መምሪያ ስራ አስኪያጅ በመሆን እንዲሁም ከሚያዚያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ በመስራት በአጠቃላይ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ ብር 715 ሺህ 190 ብር እንዲከፈለው በማድረግ በተጠቀሰው የገንዘብ ልክ ጥቅም ያገኘ መሆኑ ተመላክቶ በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎችን መርምሮና አመዛዝኖ በተከሳሹ ላይ የጥፋተኛ ፍርድ በመስጠት እንዲሁም የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ከግምት ውስጥ በማስገባት ተከሳሹን በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ110 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.